Contact me

  • Contact me via hawiti@yahoo.com or hawiolani@gmail.com

Sunday, March 2, 2014

ይድረስ ለፕ/ር ጌታቸው ሀይሌ – ታሪክ ተማሩ እንጂ፣ ከታሪክ አልተማሩም::

Posted: Bitootessa/March 2, 2014 · Finfinne Tribune | Gadaa.com | Comments (2)
ዕርቅና ሰላም፤ የሕይወት ቅመም” በሚል አርዕስት የጻፉትን ጽሁፍ ካየሁ በኋላ፣ ትምህርት መማር ብዙዎችን የማይለውጥ መሆኑን ተረድቻለሁ:: ልክ ከ18ኛ ክ/ዘመን በፊት ያሉ ሰዎች የሚያስቡት ዓይነት፣ የወረደ ጽሁፍ በ21ኛ ክ/ዘመን ከፕ/ር አልጠበኩም:: በድሮ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ከመካከለኛ ምስራቅ የመጣውን ሃይማኖት መቀበል፣ በራሱ ሥልጣኔ ይመስላቸዉ ነበር:: የድሮ ሰዎች ጥሩ አማርኛ የተናገረ “የሰለጠነ”፣ ጥሩ አማርኛ መናገር ያልቻለ “ኋላ ቀር” ብለው ያስቡ ነበር:: የ21ኛ ክ/ዘመን ፕ/ር ለዚያውም በምዕራቡ ዓለም የኖሩ ፕ/ር ይህንኑ ሲደግሙልኝ ታድያ ለምን አልገረም? ገና “‘የመሬት ላራሹ’ ጩኸት” ሲሉ ነው፣ እኝህ ሰውዬ ፊውዳል ናቸው ማለት ነው ብየ የተጠራጠርኩት:: ለማንኛውም፣ እስኪ የፕ/ሩን ፅሁፍ ይዘት ወደ መገምገም ልመለስ::
1. “ኢትዮጵያን ያቆረቆዟት እስላሞችና ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ናቸው፥ ስለሆነም ዕርቅ ይመጣ ዘንድ እስላሞችና ኦሮሞዎች አባቶቻቸው ላደረሱት ጥፋት የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው” ብለዉ አረፉ::
የኦሮሞ ህዝብም ሆነ የእስልምና እምነት ተከታዮች ኢትዮጵያ በምትባለው ሀገር ውስጥ፣ ከጥንት ጀምሮ የተበደሉ ናቸው፡፡ በዚያን ዘመንም ቢሆን ሌሎችን ለመዝረፍ እና ለማስገበር የሚዘምቱት የደጋማዉ የክርስቲያን መንግስት ገዥዎች ናቸዉ፡፡ ይህንን በተደጋጋሚ ሲፈፅሙ ኖረዋል፡፡ በተረትም መልክ “ለሰማይ ምሰሶ የለው፤ ለእስላም (ጋላ) አገር የለው” እያሉ ሲያጠቁት የነበሩት እነሱ ናቸው፡፡ ይህ እርሶ አሁን ያንፀባረቁት የጥላቻና የጠላትነት አመለካከት፣ አሁን የተጀመረ አይደለም። አባ ባህርይም “በታሪክ ጠላቶቻችን የሆኑት እስላም እና ጋላ” በማለት ጽፏል:: አፄ ቴዎድሮስ ከመነሻው ጀምሮ ሁለት ጠላቶች እንዳሉት፣ እነዚህም ኦሮሞዎች እና እስላሞች እንደሆኑ በግልፅ አውጆ ይህንኑ የወሎ ኦሮሞዎችን በመፍጀት አሳክቷል፡፡ ለንግስት ቪክቶሪያ በፃፈው ደብዳቤ መሳሪያ የሚፈልገውም እነዚህን ለመፍጀት እና ለማስገበር መሆኑን ገልጿል፡፡ (አፄ ቴዎድሮስ የሚያውቀው ጠላቶቹ የወሎ አሮሞዎች ነበሩ):: አፄ ዮሃንስም ቢሆን የወሎ ኦሮሞዎችን ወይም እስላሞችን፣ ቦሩ ሜዳ ላይ ሰብስበው በሺዎች የሚቆጠሩትን እጃቸውን መቁረጡ ይታወቃል፡፡ እነሱ ለፈፀሙት፣ ኦሮሞና እስላም ይቅርታ ሊጠየቁ ሲገባው፣ እንዴት ይቅርታ ይጠይቁን ይባላል?
አጥፍቶ  ከሆነ  ይቅርታ መጠየቅ ለኦሮሞ ምንም አስቸጋሪ አይደለም:: በኢትዮጵያ ታሪክ ከሥልጣን ወርዶ ሕዝብን ይቅርታ የጠየቀ ከዶ/ር ነጋሶ ውጪ አለን? ይህ እንግዲህ ሥልጣኔ ነው:: ሥልጣኔ ቤት መገንባት እና ድንጋይ ማቆም ብቻ ነው ያለው ማነው? ዋናው ጥያቄ ግን ጥፋቱ ምንድነው? የሚለው ነው:: ፕ/ሩ  ኦሮሞ አገር የለውም ባይ ናቸው:: ይህ እንግዲህ ሃበሾች ኦሮሞን በአገሩ ሄደው ሲያጠቁ ለማስገበርም ሆነ አገሩን ለመቀማት  ሲዘምቱበት  የሚያቀርቡት  ምክንያት ነው::  እውነት ኦሮሞ አገር የለውም እንዴ?  ነው ወይስ ከማዳጋስካር ነው የመጣው? “ኦሮሞ ከአፍሪካ ቀንድ ውጪ መጣ” የሚሉት ታሪክ የውሸት ታሪክ ነው። የኩሽ ነገድ ህዝብ ከግብፅ ጀምሮ በዛሬይቷ ሱዳን እና በአፍሪካ ቀንድ ለብዙ ሺህ ዓመታት በመኖሩ ይህ አካባቢ ለኩሾች ጥንት መኖሪያቸው ነው፡፡ ከ700 ዓመተ አለም እስከ 100 ዓ.ም ከየመን ፈልሰው ወደ አፍሪካ ቀንድ የመጡት አግዓዚያኒ የተባሉት የሴም ዘሮች ናቸው፡፡ እነዚህ ናቸዉ እንግዲህ ነባሩንና አፍርካዊውን የኦሮሞ ህዝብ መጤ ነው የሚሉት:: የኩሽ ነገድ የሆኑት እነ ሲዳማ፣ ሀዲያ፣ አፋር፣ ሱማሌ፣ አገው፣ ሁሉ አገራቸሁ የአፍሪካ ቀንድ መሆኑ እየታወቀ ኦሮሞ ብቻ መጤ የተባለው ልያስገብሩት ሲዘምቱበት ስላልተሣካላቸዉ ነው:: ሊወሩትና ሊዘርፉት ሲመጡ አሸነፋቸው:: መሬታቸውን አባሮ ያዘባቸው:: ራስን መከላከል (self defense) በአለማቀፍ ህግ የተረጋገጠ መብት ነው:: ፕ/ር ጌታቸው “ኦሮሞ አልገብርም ብሎ” ብለዋል:: አዎ ትክክል ነው:: በሃገሩ ላይ ለራሱ የገዳ መንግስት እንጅ ለእነ ሀምደፅዮን ለምን ይገብር? ጉዳዩ “ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሀል” ሆነ እንጂ ይቅርታ መጠየቅ ያለበት ወራሪው ነው::
2. “አፄ ምኒልክና ራስ ጎበና ዳጨ ስፍር ቁጥር በሌለው ጎሳ የተበታተኑትንና እርስ በርሳቸው የሚባሉትን ኦሮምኛ ተናጋሪዎች አንድ ያደረጉበትን ቀን በየዓመቱ ማክበር አለባቸው።”
አፄ ምኒልክ ምን አደረጉ?
1. ቡላቶቪች የተባለው ራሺያዊ በ1900 ከሚኒሊክ ጦር ጋር ዘምቶ የነበረ ሲሆን “Ethiopia Through Russian Eyes” በተሰኘው መጽሀፉ የሚኒሊክ ወረራ የኦሮሞን ህዝብ ቁጥር በግማሽ ያሳነሰ መሆኑን ጠቅሷል፡፡
2. ማርቲን ዴ ሳልቫክ የተባለ ፈረንሳዊ የካቶሊክ ሚሺነሪ (1900) “The Oromo: An Ancient Africa Nation” በተባለው  መጸሀፋቸው  በዚህ  ወረራ  የኦሮሞ  ህዝብ  ቁጥር  በግምት ከአስር  ሚሊየን  ወደ  አምስት  ሚሊየን መውረዱን ገምቷል፡፡
3. August 18, 1895 እ.አ.አ የታተመው የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ፣ አፄ ሚኒሊክ በኦሮሞ ላይ ዘመቻ በመክፈት ወንዶቹን በመፍጀት ሕፃናት እና ሴቶችን በባሪያነት መውሰድ በሰፊው ይተገበሩ እንደነበር ፅፏል፡፡
4. February 26, 1895 እ.አ.አ የታተመው የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ አሰቃቂው የሚኒሊክ ዘመቻ በሚል ርዕስ ስር ሰሞኑን ንጉስ ሚኒሊክ በኦሮሞ ህዝብ ላይ በደቡብ አቢሲኒያ የከፈቱት ዘመቻ 70,000 ሰዎችን በመግደል 15,000 መማረካቸውን ገልፀዋል፡፡
5. August 2,1874 እ.አ.አ የታተመው የኒውወርክ ታይምስ ጋዜጣ የአቢሲንያ ባሪያዎች በሚል አርስት ስር በየዓመቱ ከ80,000 እስከ 90,000 የሚሆኑ ባሪያዎች በምፅዋ ወደብ በኩል ወደ ውጪ የሚሽጡ መሆኑን ጠቅሶ የባሪያ ነጋዴዎቹ ባሪያዎችን የሚገዙት ከነፍጠኞቹ ሲሆን ንጉሰ ነገስቱም የቀረጡ ተቋዳሽ መሆኑን ያትታል፡፡ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጽያዊያኖችን በባርነት ሸጠዋል (መኩሪያ ቡልቻ)::
6. አኖሌ ላይ የሦስት ሺህ ኦሮሞዎች እጅ እና ጡት ከማስቆረጣቸው በተጨማሪ በአደዋ ጦርነት የተማረኩ 800 የኤርትራ አስካሪዎችን ቀኝ እጅ እና ቀኝ እግር አስቆርጠዋል፡፡
7. November 7, 1909 እ.አ.አ የታተመው የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በአርስቱ የአቢሲኒያው ንጉስ ሚኒሊክ በአሜሪካው የባቡር ሃዲድ ስራ ተቋራጭ ከፍተኛ የአክሲዮን ባለቤት ናቸው በማለት ወደ ዝርዝሩ ውስጥ ስንገባ ይህ የባቡር ሃዲድ አክሲዮን ከሃያ አምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ መሆኑ እና ከዚህ በተጨማሪ በቤልጅየም እና እስካንዲኒቭያ ከተሞች የወርቅ አምራች ኩባንያ ውስጥ አክሲዮን እንዳላቸው ዘርዝረዋል፡፡ ይህ ሁሉ ንብረት ከዬት መጣ ብለን ብንጠይቅ ከተወረሩ ብሄር ብሄረሰቦች የተዘረፈ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በዚሁ መሰረት የሚኒሊክ ወታደሮች ከአርሲ 66,000 የቀንድ ከብት (ፕሮፌሰር መኩሪያ ቡልቻ)፤ ከወላይታ 18,000 (ተሻለ) ከደቡብ ኦሞ 40,000 ከጂጂጋ 50,000 (ጆን ማርካኪስ) ወዘተ… የተዘረፈ ነው፡፡
8. አፄ ሚኒሊክ ከምእራብ ኢንዲያ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ የጥቁር ህዝብ መሪ ሁንልን ብሎ የጠየቀውን ቤኒቶ ሲልቪያን የተባለውን ሰውዬ እኔ ጥቁር አይደለሁም፡፡ ሴማዊ ነኝ በማለት አባረውታል፡፡ ሀይለስላሴም HO Davis የተባለው ታዋቂው የጥቁር መብት ታጋይ እና Marques Garvey የተባለው ጃማይካዊ የጥቁር መብት ታጋይ ባናገሩት ጊዜ እኔ የሰለሞን ዘር ነኝ በማለት አፍሪካዊነታቸውን ክደዋል፡፡ እነዚህ በአፍሪካዊነታቸው የማያምኑ፣ በአፍሪካዊነታቸው የሚያፍሩ የበታቸው ስነ ልቦታ የተጠናወታቸው እና በራሳቸው የማይተማመኑ ናቸው፡፡
9. በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ኦሮሞ ሁሉ ተገዛ፣ በአማራ ሕግና ሥርዓት ሔደ፣ ካህናቱ አንድ ኦሮሞ አስተምረው አላጠመቁም፡፡ ይልቅስ ተፊተኛው ቂም የበለጠ ቂም በልቡ አኑረውበት መሬቱን በቀላድ ወሰዱበት፡፡ አንድ ቀላድ የቅስና አንድ ቀላድ የአወዳሽ እያሉ በዚሁ ስብከት ንጉሡን አሳመኑ፡፡ ስለ መንግሥት ያሰቡ መስለው ለንጉሡም አንድ ቀላድ፣ ለወታደር አንድ ቀላድ … መሬቱን ተካፍለው ኦሮሞን እንደ ባሪያ አድርገው ይገዙታል እንጂ የክርስቶስን መንገድ አላሳዩትም፡፡ እነርሱም የእግዝሔርን መንገድ በሚገባ አልተማሩም፣ አስተማሪም ቢመጣም ይከለክላሉ …፡፡ (አፅሜ ጊዮርጊስ )
ይህ ሁሉ ግፍ የተፈፀመባቸዉ ኦሮሞዎች እንዴት ይስገዱለት ይባላል?
ኦሮሞ ከአንድ የዘር ግንድ የተገኘ አንድ ህዝብ ነው፤ የቦረና እና የባሬንቱማ ልጆች:: የቦረና እና የባሬንቱማ ልጆች ህዝባቸው በመብዛቱና አገራቸው በመራራቁ በተለያዩ ገዳዎች ስር መተዳደር ጀመሩ፡፡ በዚህም መሰረት የቦረና ኦሮሞዎች ኦዳ ነቤን ማእከላቸው ሲያደርጉ ባሬንቱማዎች ደግሞ ማእከላቸውን ኦዳ ቡልቱም አድርገዋል፡፡ በተለያዩ ገዳ ሥር የተከፋፈሉ ኦሮሞዎች አልፎ አልፎ የጎሳ ግጭቶች በመካከላቸዉ ሊፈጠር ይችላል:: ይህንን ግጭትም በጉማ ይፈቱት ነበር። ፕ/ሩ እንዳሉት በጎሳ የሚጋጩ ወይም በጎሳ የተደራጁትን መውረር መጨፍጨፍ እና መፍጀት በጎ ተግባር ነው ከተባለ አውሮፓውያን አፍርካን መውረራቸውን የምንቃወመው ነጭ ስለሆኑ ብቻ እንጅ በጎሳ የሚጋጩ አፍሪካውያንን መውረራቸው በጎ ተግባር ነበር ማለት ነው።
የገዳ ስርዓት የሥልጣኔ ምልክት እንጂ የማፊያ ሥርዓት አይደለም:: ሥርዓቱ ስልጣን ከአንድ ቡድን ወደ ሌላ ቡድን በሰላማዊ  መንገድ የሚተላለፍበት ስርዓት ነው፡፡ ይህ ስርዓት በየስምንት ዓመት እድሜ እርከን የስራ ድርሻ በመከፋፈል ህብረተሰቡን በአምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ስር በማደራጀት አምስቱ ቡድኖች ተራ በተራ ለስምንት ዓመት የሚያስተዳድሩበት ስርዓት ነው፡፡ ሁሉም ሉባ የራሱ የሆነ የሚያከናውነው ተልዕኮ አለው፡፡ ለምሳሌ በጠላት የተያዘ መሬት ካለ የማስለቀቅ ግዴታ ስለሚኖርበት ያንን ጉዳይ እስካላከናወነ ድረስ እረፍት አይኖረውም፡፡ እነ  አባ ባህሪ  በስርዐቱ  ጥንካሬ ምክንያት በወገኖቻቸዉ ላይ በደረሰው ሽንፈት የተነሳ የቻሉትን ያህል ስርዐቱን አሉታዊ አስመስለው  ስለፃፉ  የስርዐቱን ዲሞክራሲያዊነት አያሳጣውም፡፡  የገዳ ስርዐት  የኦሮሞን  ህዝብ  በእኩልነት  እና በዲሞክራሲ እንዲኖር ያስቻለና በተሻለ አደረጃጀት የኦሮሞ ህዝብ ራሱን እንድከላከል ያስቻለዉ በመሆኑ የኦሮሞን  ህዝብ የሚጠሉ  “አባ  ባህሪዎች” እና ተሸናፊዎች  ይህንን  ስርዐት  ሊወዱት  አይችሉም፡፡
እኛ ኦሮሞን አንንቅም አንጠላም ይሉ ይሆናል።‹‹ራእየ ማርያም›› ከሚል የጸሎት መጽሐፍ ኮፒ የተደረገ ጽሑፍ ላስነብቦት:
“… ከስር እስከ ጫፍ፣ ከጫፍ እስከ ስር ድረስ በአምስት ሺሕ ዓመት የማይደረስበት ትልቅ ገደል አሳየኝ፡፡ ያንዱ ነፍስ በአንዱ ላይ ሲወድቅ ዐየኹ፡፡ እኔም ምንድናቸው ብዬ ልጄን ( ኢየሱስን መኾኑን ልብ ይሏል) ጠየቅኹት፡፡ እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላት፡­ … አራስ፣ መርገም፣ ደንቆሮ፣ ‹‹እስላም››፣ ‹‹ጋላ››፣ ‹‹ሻንቅላ››፣ ‹‹ፈላሻ›› ጋር የተኙ፣ ፈረስ፣ አህያ፣ ግመል በግብረ ስጋ የሚገናኙ፣ ወንዱም ግብረ ሰዶም ወገሞራ የሚዳረጉ… እነዚህ ሁሉ ኩነኔያቸው ይህ ነው አለኝ …፡፡”
በአንድነት የእግዚአብሔርን መንግሥት እንወርሳለን ብላ በምታስተምር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሕዝቦችን የሚለያይና የሚከፋፍል ጽሑፍ መኖሩ ምን ይባላል እስኪ? እኛ ይህንን ሁሉ ችለን ነዉ እርቅና ሰላም ይሻላል ብለን የተቀመጥነዉ።
ስለ መስለብም አንስተዋል። መስለብ የሰሜቲኮችና የአማራ ባህል ነው። ማስርጃ ፩። በመጽሀፍ ቅዱስ መጽሀፈ ነገስት ውስጥ ዳዊት የሳኦልን ልጅ ለማግባት የ200 ፊልስጤማውያን ብልት ቆርጦ ማምጣቱ:: ዳዊት የሰለሞን ኣባት ነው። የሰለሞን ልጆች ነን የሚሉት እነማን እንደሆኑ ማስረዳት አይጠበቅብንም። ማስርጃ ፪። በመጽሀፍ ቅዱስ የሀዋርያት ሥራ መጽሀፍ አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዞ ነበር። ይህ ግዜ በግምት ፩ኛ ክፍለ ዘመን ነው። ሰውየው ከሰሜን ኢትዮጵያ ስለመሆኑም ግልጽ ነው። ማስርጃ ፫። ኮሎኔል አልኸንድሮ ዴል ባየ የተባለው የኢትዮጵያ ወዳጅ በጻፈው “ቀይ አንበሣ” በተሰኘው መጽሀፍ ውስጥ አማሮች ከ10 እስከ 15 ዕድሜ የሆኑ ህጻናትን ብልት እየሰለቡ የንጉሶች፣ የራሶች እና የፊታውራሪዎች አገልጋይ ጃንደረባ ያደርጓቸው እንደነበር ጽፏል። ድምጻቸው ወደ ቀጭንነትም ስለሚቀየር ቤቴ ክርስቲያን ውስጥም ይቀድሱ እንደነበር ይታወቃል።
3. “ሶስተኛው እርምጃ አስተሳሰብን ከሰብአ ትካት አስተሳሰብ ወደ ሰብአ ዘመን አስተሳስብ ማራመድ ነዉ”
አባ ባህሪ ብእራቸውን ከወረቀት ጋር  ሲያገናኙ  የነገዱን ቁጥር  ብዛት ፣ ሰውን ለመግደል ያለውን ትጋት ወዘተ እያሉ በጥላቻ እና በጠላትነት መንፈስ ልክ እንዳንተ የፃፉ በመሆናቸው እንደ እውነተኛ ታሪክ አድርገህ ልትከራከርባቸው መሞከርህ የታሪክ ምሁርነትህን አጠያያቂ ያደርገዋል:: የኢትዮጵያ ታሪክ የውሸት ታሪክ ነው። ባለሟሎቹ ነገስታቱን ለማስደሰት ልክ ዛሬ የመለስ ደጋፊዎች “የተለየ ራዕይ ያለው፣ መልካም መሪ”፣ በሚሊዮን ዓመት አንዴ  የተፈጠረ፣”  ወዘተ… እያሉ እየፃፉለት እንዳሉት ያኔም ንጉሶቹን  በማሞገስ  ጽፈውላቸዋል። ጠላቱን ደግሞ በማውገዝ ያስደስቱታል። እንድያውም የኢትዮጽያ ታሪክ ክብረ ነገስት ይባል የለም?
የኩሽ   ሥልጣኔ   በአፍርካ   ቀደምትሥልጣኔ   መሆኑን   Drusilla   Dunjee   Houston,   (1876­1941)Wonderful Ethiopians በተሰኘዉ  መጽሃፏ the  Cushites  were the earliest known Black African civilization. Reaching its peak between 1750 and 1500 B.C.E., and lasting until the fourth century C.E., the Cushite empire occupied what is now the Sudan, with its capital at Meroe on the Nile. At their high point, Cushites even conquered and ruled ancient Egypt from 750­650 B.C.E. Because of their geographical isolation, they had nowhere near the impact on other parts of the world that Houston attributed them. The Cushites were heavily influenced by the older Egypt culture, rather than  the  other  way around. They left behind fields of hundreds of small steep­angled burial pyramids,  the  design  of  which  was borrowed from Egypt and scaled down. በማለት ይህ ሕዝብ የታላቅ  እና  የቀደምት  ሥልጣኔ  ባለቤት  መሆኑን  አብራርታለች።    Pre­historic  Nations  በተሰኘዉ መጽሃፉ John
D. Baldwin (1809­1883) የኩሽ ሥልጣኔ ከግብጽም ይቀድማል በማለት ጽፏል­ “According the author, there was an ancient civilization that existed in Ancient Arabia, prior to the rise of the civilizations in Sumer, Egypt and the Indus Valey.”ኩሽ (ጥቁር ፌሮኖች)ግብጽን ስያስተዳድሩ እንደነበርም ­ In 1913 to 1916 Harvard Egyptologist George A. Reisner (1867­1942) discovered a previously unknown Sudanese civilization and the first archaeological evidence that Cushite kings ruled Egypt.
ለመሆኑ ስልጣኔ ማለት ምን ማለት ነው? ስልጣንን በሰላም ማስተላለፍ ነው ወይስ ለስልጣን ብሎ መጨራረስ እና መፈጃጀት? በዘመነ እያሱ በጎንደር ቤ/መንግስት የመርዝ ሰለባ የሆኑትን ታሪክ ይቁጠራቸው፡፡ ለበቀል አለመገዳደል እና የጠፋ ህይወት ሲኖር በጉማ መጨረስ ስልጣኔ አይደለም ወይ? ሚስቴን አየህ በሚል ከመገዳደል እና በሴት ጉዳይ አንገዳደልም ብሎ ህግ ከማውጣት የቱ ነው ዘመናዊነት? ኦሮሞዎች በሴት ጉዳይ እንደማይገዳደሉ በእርሶ መጽሐፍ ተጽፏል:: አማራዎች ግን ከሚስቶቻቸው ውጭ ሌላ ሴት ሲያፈቅሩ ሚስቶቻቸውን በመርዝ ገድለው ሌላ ያገቡ እንደነበር ያነበብኩት ከዚሁ ከመጽሐፍዎ ነው፡፡ ኦሮሞዎች ለህጎቻቸው በጣም እንደሚገዙ፣ በሸንጎዋቸው በውሸት እንደማይፈርዱ እንዲሁም በውሸት እንደማይምሉ የአለቃ ታዬ መጽሀፍ ላይ ተጽፏል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን የውጪ ሀይል በሚያጠቃቸው ጊዜ ድንበራቸውን ለመከላከል በገዳ አደረጃጀት መሰረት እራሳቸውን ይከላከሉ ነበር:: በዚህ ወቅት የወጋቸውን ጠላት ለምን ገደሉ? ማለት አይቻልም:: ይህ በማንኛውም መንግስታት መካከል በሚደረጉ ግጭቶች እንኩዋን የተለመደ ነው፡፡ ለመሆኑ እርሶ የሚመፃደቁበት ስልጣኔ ቤተ ክርስቲያን ከመሄድ እና ታቦት እና መስቀል ከመሳለም የዘለለ ምን ተጨባጭ ነገር ሊያሳዩን ይችላሉ?  አሁንም ድረስ ከስማችሁ ጀምሮ ደመላሽ፣ አሸብር፣ ግዛው፣ እርገጤ፣ ሽናባቸው፣ ድፋባቸው ወዘተ… እየተባለ የመገዳደል፣የበቀል እና የሽብር ስሞችን ነው የምናየው፡፡ ባህላችሁም ቢሆን ለሰብአዊ ፍጡር ርኅራሄ የሌለው፤ አንዱን ሌላውን የመርገጥ፤ ልክ ሰሞኑን በባህር ዳር እንደታየው ሰው/ባርያ መሸጥ እና ፊውዳላዊ ስርዐት እንጂ ሠላማዊ ሆኖ አያውቅም:: እኔ እስከማቀው ድረስ ስልጣኔ ታማኝነት ነው፡፡ ኦሮሞ ታማኝ መሆኑን ደግሞ ሰሞኑን ማንዴላን ከሞት ያተረፉት መቶ አለቃ ጉታ ዲንቃ እና ጄኔራል ታደሰ ብሩ ማሳያ ናቸው:: ከድሮ ጀምሮ በነበሩት ስርዓቶች ኦሮሞዎች ላመኑበት ከመቆም ውጪ ክህደትን የማያውቁ፣ ቃላቸውን የማያጥፉ መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡ ለስልጣን ሲባል ህዝብህን ማስፈጀት እና መተላለቅ በምንም አይነት ስልጣኔ ሊሆን አይችልም፡፡ ቅንነት፣ ቤተሰብን መውደድ፣ እራስን ከፍ ከፍ ያለማድረግ የስልጣኔ አንጂ የኃላ ቀርነት ምልክት ሊሆን አይችልም፡፡ ዘላንነትን (አርብቶ አደርነት) የአኗኗር ዘይቤ እንጂ ኋላ ቀርነት አይደለም:: ክርስቲያን  አለመሆን ወይም  በአፍሪካዊ  እምነት  (ዋቄፈና) ተከታይ  መሆንም  ቢሆን  ሊደነቅ  እና  ሊኮራበት የሚገባ እንጂ     እንደ      ኋላቀርነት           ሊታይ    አይችልም፡፡  የራስ  የሆነ የእምነት ፍልስፍና የዛን ህዝብ  ታላቅነት የሚያሳይ ነው፡፡
ደቡብ ሱዳኖች ራሳቸዉን አረብ እና የበላይ አድርገዉ የምያስቡትን ሰሜን ሱዳኖችን  መታገላቸዉ ሰብአ ትካትነት ነበርን?ስኮትላንዶች ከብሪትሽ መገንጠላቸዉ ሰብአ ትካትነት ነበርን? የኮሶቮ አልባንያዎችስ ሰብአ ትካት ናቸዉን? ካልጨቆንኩ፣ በሀብትህ እና በተፈጥሮ ሀብትህ ላይ ካላዘዝኩ፣ ማንነትህን ፣ቋንቋህንና ባህልህን ካላጠፋው ሞቼ እገኛለው የሚልህን ሀይል መጥላት ብቻ ሳይሆን መውጋት ተገቢ ነው፡፡ ኦሮሞ ከኔ ብሄር ውጪ ሌላ ብሄር መኖር የለበትም አይልም፡፡ ከሌሎች ጋር በሠላም እየኖረ ነው፡፡ ወደፊትም በሠላም ይኖራል፡፡ ነገር ግን  የጨፈጨፈውን እና ያዋረደውን ስርዐት እያሞገሱ እና በአያቶቹ አፅም እና እሬሳ ላይ ካልጨፈርን የሚሉትን፤ እኛ ምን ግዜም የበላይ ነን የሚሉትን፤ ምንም ቴክኖሎጂ (ስልጣኔም) ሳይኖራቸው በባዶ ሜዳ እራሳቸውን ሰቅለው የሚንቁትን አይታገስም:: አሁን የተጎናፀፈውን በክልሉ ላይ እራሱን በራሱ የማስተዳደር፣ ቋንቋውን የመጠቀም ጉዳዮች ላይ (ምንም እንኩዋን ሀቀኛ ባይሆንም) ይህንን ሀቀኛ ለማድረግ ይታገላል እንጂ አንዳች ቅንጣት ወደ ኋላ እንዲመለስ አይፈቅድም::
ዴሞክራሲ ስለ ግለሰብ መብት ብቻ አይደለም። የቡድን መብቶችንም ይይዛል። በዚህም የተነሳ ነዉ የግለሰብ መብት ላይ  ብቻ  ከሚያተኩረዉ Universal Declaration of Human Rights (UDHR) ይልቅ International Covenants on Civil and Political Rights (ICCPR) ተቀባይነት ያገኘዉ።
በአጠቃላይ የተማሩና የተመራመሩ ፕሮፌሰር ለአንድ ብሄር እና ለአንድ ሃይማኖት የበላይነት ሲቆሙ የራስን ማንነት፣ ቋንቋ እና ባህል እንዲሁም እራስን በራስ የማስተዳደር አለም አቀፋዊ መብት ይከበርልን የሚሉ ወገኖችን “ሰብአ ትካት” በማለት መሳደባቸው በእጅጉ የሚያሳፍር ዘረኝነት ነው፡፡ የራስን መብት መጠየቅ ከሌላው ጋር እኩል ነኝ ማለት የሌላውን ሳያንቋሽሹ እና ሳይንቁ የራስን ማሳደግ ጤነኛ ብሄርተኝነት ነው፡፡ ይህ በምንም መልኩ ሊያስወቅስ አይችልም:: እርስዎ ምንአልባት በወጣትነትዎ ዘመን የፊት አውራሪ እገሌ ዘር ወይንም የመሳፍንት ዘር በማለት የተወሰኑ ሰዎች በዘር የበላይነት እና ልዩ ጥቅም የሚያገኙበትን ሁኔታ ተጠቅመው የነበሩ እና አሁንም ያንኑ የሚያልሙ ይመስለኛል:: እና ያ እርሶ የሚያልሙት የአንድ ዘር የበላይነት እና ሌሎችን የተለያያ ስም በመስጠት ከሰው የበታች እንደሆኑ አድርጎ ማሰብ ግዜው ያለፈበት በመሆኑ ታሪክ መማርዎ ብቻ በቂ አይደለምና የዚህ አይነት አመለካከት የነበራቸው ከሮማን ኢምፓየር እስከ ብሪትሸ ኢምፓየር እና ናዚ ድረስ በሙሉ ወድቀዋልና ከታሪክ ይማሩ ብለን እንመክሮታለን፡፡

No comments:

Post a Comment