ከከተማ ዋቅጅራ*
ግፉ በአስቸኳይ ይቁም። በየአካባቢው ያለ ምክንያት የሚገደሉ ዜጎች አይኑሩ። በየመንደሩ ማዋከብ ይቁም። እስር ቤቶች የንጹሃን ዜጎች ማሰቃያ አይሁን። እውነትን በሐሰት ለመለወጥ አትሞክሩ … ወርቅን በጠጠር እንደ መለወጥ ነውና። ምክንያት እየፈጠራችሁ ግፍና በደልን አትፈጽሙ … ፈሪ ሃይልን ያበዛልና … ሃይልን ከመጠቀም እና የከፋ በደል ከመስራት ተቆጠቡ። ዛሬ ለጥቂቶች ብርሃን ቢመስላቸውም ነገ እንደሚጨልምባቸው እወቁ። ዛሬ ለጥቂቶች ብዙሃኑን እረግጠው የነጻነት ቀን የመጣ ቢመስላቸውም ነገ ብዙሃኑ አሸንፎ ነጻነቱን ሲያውጅ ለጥቂቶች እንደሚጨልምባቸው እወቁ። ከጥቂቶች ጋር በማቀንቀን የግፍ ጽዋን አታንሱ … ከብዙሃኑ ጋር የእውነትን መራራ ሕይወት ተጋሩት እንጂ። ምክንያቱም ግፈኞች የሚኖሩት ለጥቂት ግዜ ነውና … ህዝብ ግን ለሁሌ ስለሆነ ከህዝብ ጋር አትጣሉ እናንተ የወያኔ ተላላኪዋች።
ዘርተን አብቅለን መገብናቸው የሚጠጡትንም አቀረብንላቸው መልሰው በጥጋባቸው እኛኑ እየረገጡን አላስቀምጥ አሉን። ጥጋባቸው ቁንጣን ሆነባቸው። ወያኔ ጋር የሚፈላ ደም እንጂ የሚያስተውል ልቦና እንደሌለ አወቅን። የወያኔ ስጋት ከልክ በላይ ደርሶ እንቅልፍ ካሳጣው ሰነባብቷል። በአሁኑ ግዜ ዞሮ ማየት በነጻነት መናገር እንደ ወንጀል ተቆጥሯል። እውነት ሲነገራቸው አይወዱም … ስለ ነጻነት እንዲነሳባቸው አይፈልጉም። እውነት ያስፈራቸዋል ነጻነትም ያንገሸግሻቸዋል። ከዚህ እውነት ለመሸሽ እናንተ ‘ጠባቦች’ … እኛ ነን ሰው ያደረግናችሁ … እኛ ነን እድገት ያመጣንላችሁ … እኛ ነን ነጻነትን ያመጣንላችሁ … ይሉናል በቀጣፊ አንደበታቸው አይናቸውን በጨው አጥበው። እኔ አልገባኝ ይሆን? ምንድነው ነጻነት? እድገትስ ምን ማለት ነው? ስታስነጥስ ይሄ የአሸባሪ አነጣጠስ ነው ብለው በፈሪ ዱላ እየቀጠቀጡ ወደ ወይኒ ማጋዝ ነው? … ወይስ ብዕር ስታነሳ ይሄ የአሸባሪ ብዕር ነው እያሉ ወይኒ ማውረድ ነው። ነጻነት ምንድ ነው? እድገትስ ምን ማለት ነው? የአይንህ ቀለም አላማረኝም ተብሎ አሸባሪ ነህ እያሉ በፈሪ ዱላ መቀጥቀጥ ነው። ወይስ ለጥቂት ተላላኪዎች እና ለወያኔ ሰዎች የህዝብን ንብረት ዘርፈው በህዝብ ሃብት ህንጻ መቆለል ነው? ኽረ የቱ ነው እኔ አልገባኝም? አገሪቷን ከአለም አንደኛ የብድር እዳ ያለባት አገር ማድረግ ነው? ወይስ በየቦታው ስደተኛን እና ችግረኛን ማብዛት ነው? ወይስ ዜጎች በአገራቸው መብት አልባ አድርጎ ማኖር ነው? ወይስ ከላይ እስከ ታች እንደ ሰንሰለት በተጠላለፈ ካድሬ መጠርነፍ ነው እድገት እና ነጻነት? ምንድነው ነጻነት? በነጻነት ካልኖሩ በነጻነት ካልሰሩ በነጻነት ካልተናገሩ በነጻነት ካልዘመሩ ነጻነቱ ምኑ ላይ ነው?!
ህዝቡ ነጻነቱን ያገኘች አገር ቢሆን ኖሮ ህዝቡ በነጻነት የመስራት እና የመንቀሳቀስ መብቱ የተጠበቀ ቢሆን … ሁሉም በሙያው ያለ ሙስና እና ያለ አድሎ በእውቀቱ በችሎታው ቢሰራ … ህዝብ የወደደው መሪ በህዝብ የተመረጠ እና የተወደደ መሪ ቢኖራት አሁን ወያኔ አድጋለች ብሎ ከሚነግረን በሚታይ እድገት ሞቶ እጥፍ ከደስታ ጋርና ከሰላም ጋር ታድግ ነበረ … ህዝብ ላይ እንደመዥገር ተጣብቀው የጥቂቶች እድገት እና ሰላም ታውጆባት የግፈኞች በደል ህዝባችን ላይ ተጭኖ ለመኖር ተገደድን። ሰላምን ያጣ እና ነጻነቱን የተነፈገ ህዝብ በጀግንነቱ ነጻነቱን እንደሚመልስ የታወቀ ነው። ወያኔ ሆይ ህዝባችን ጀግና መሆኗን አትዘንጋ።
ፈሪ ሁሌም ሃይልን ያበዛል። የፈሪ በትሩ አንድ ሺ ነው እንዲሉ። ጀግና ደግሞ ዝም ይላል ይታገሳል ዝምታውን ሰብሮ ትግስቱ ያለቀ እለት … የወያኔን የፈሪን ጅስም ሰብሮ ጀግናው ህዝብ ጅስሙን ያሳየሃል። ለዚህም ደግሞ ተዘጋጅተናል። ግዜው የድል ነው።
* ከተማ ዋቅጅራ: waqjirak@yahoo.com
No comments:
Post a Comment